ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 11

1 ፤ መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደሚመለከት ወደ እግዚአብሔር ቤትም ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ። እነሆም፥ በበሩ መግቢያ ሀያ አምስት ሰዎች ነበሩ፥ በመካከላቸውም የሕዝቡን አለቆች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስ ልጅ ፈላጥያን አየሁ።
2 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ክፋትን የሚያስቡ በዚህችም ከተማ ክፉን ምክር የሚመክሩ ሰዎች ናቸው።
3 ፤ እነርሱም። በውኑ ቤቶችን የምንሠራበት ዘመን የቀረበ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት እኛም ሥጋ ነን ብለዋል።
4 ፤ ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር።
5 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ወደቀብኝ እንዲህም አለኝ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህን ነገር ተናግራችኋል፥ እኔም የልባችሁን አሳብ አውቃለሁ።
6 ፤ በዚህች ከተማ ውስጥ ግዳዮቻችሁን አብዝታችኋል በጎዳናዎችዋም ግዳዮችን ሞልታችኋል።
7 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመካከልዋ ያኖራችኋቸው ግዳዮቻችሁ እነርሱ ሥጋው ናቸው፥ ይህችም ከተማ ድስቱ ናት፤ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ።
8 ፤ ሰይፍን ፈርታችኋል እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ ከመካከልዋም አወጣችኋለሁ፥ በእንግዶችም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ በላያችሁም ፍርድ አደርጋለሁ።
10 ፤ በሰይፍ ትወድቃላችሁ በእስራኤልም ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
11 ፤ ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፥ እኔም በእስራኤል ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
12 ፤ በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አላደረጋችሁምና፤ በዙሪያችሁም እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል።
13 ፤ ትንቢትም በተናገርሁ ጊዜ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግምባሬ ተደፍቼ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! በውኑ የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን? ብዬ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ።
14 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
15 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ራቁ፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች የሚሉአቸው ወንድሞችህና ዘመዶችህ የወገኖችህም ሰዎች ሁሉ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ናቸው።
16 ፤ ስለዚህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ወደ አሕዛብ አርቄአቸዋለሁ፥ ወደ አገሮችም በትኛቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ፥ በመጡባቸው አገሮች በእነዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ በል።
17 ፤ ስለዚህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአሕዛብ ዘንድ አከማቻችኋለሁ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች እሰበስባችኋለሁ፥ የእስራኤልንም ምድር እሰጣችኋለሁ።
18 ፤ ወደዚያም ይመጣሉ፥ ጸያፉንና ርኩሱንም ነገር ሁሉ ከእርስዋ ያወጣሉ።
20 ፤ በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
21 ፤ ልባቸውም ጸያፍንና ርኩስን ነገር በሚከተል በእነርሱ ራስ ላይ መንገዳቸውን እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
22 ፤ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ።
23 ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማይቱ ውስጥ ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል ባለው ተራራ ላይ ቆመ።
24 ፤ መንፈስም አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። ያየሁትም ራእይ ከእኔ ወጥቶ ተለየ።
25 ፤ እግዚአብሔርም ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞች ተናገርሁ።