ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 40

1 ፤ በተማረክን በሀያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ ከተመታች በኋላ በአሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ።
2 ፤ በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም ላይ በደቡብ ወገን እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር ነበረ።
3 ፤ ወደዚያም አመጣኝ፥ እነሆም፥ መልኩ እንደ ናስ መልክ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፥ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ እርሱም በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር።
4 ፤ ሰውዬውም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አሳይህ ዘንድ አንተ ወደዚህ ተመርተሃልና በዓይንህ እይ በጆሮህም ስማ በማሳይህም ሁሉ ላይ ልብህን አድርግ፤ የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር አለኝ።
5 ፤ እነሆም፥ በቤቱ ውጭ በዙሪያው ቅጥር ነበረ፥ በሰውዬውም እጅ የክንዱ ልክ አንድ ክንድ ከጋት የሆነ ስድስት ክንድ ያለበት የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ የቅጥሩንም ስፋት አንድ ዘንግ ቁመቱንም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ።
6 ፤ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተውም በር መጣ በደረጃዎቹም ላይ ወጣ፥ በበሩ በኩል ያለውንም የመድረኩን ወለል ወርዱን አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ።
7 ፤ የዘበኛውም ጓዳ ሁሉ ርዝመቱ አንድ ዘንግ፥ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ፤ በዘበኛውም ጓዳዎች መካከል አምስት ክንድ ነበረ፤ በበሩም ደጀ ሰላም በስተ ውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ የመድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ።
8 ፤ በስተ ውስጥም ያለውን የበሩን ደጀ ሰላም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ።
9 ፤ የበሩንም ደጀ ሰላም ስምንት ክንድ፥ የግንቡንም አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ደጀ ሰላም በስተ ውስጥ ነበረ።
10 ፤ የምሥራቁም በር የዘበኛ ጓዳዎች በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፥ ለሦስቱም አንድ ልክ ነበረ፤ የግንቡም አዕማድ ወርድ በዚህ በኩልና በዚያ በኩል አንድ ልክ ነበረ።
11 ፤ የበሩንም መግቢያ ወርድ አሥር ክንድ የበሩንም ርዝመት አሥራ ሦስት ክንድ አድርጎ ለካ።
12 ፤ በዘበኛ ጓዳዎችም ፊት በዚህ በኩል አንድ ክንድ በዚያም በኩል አንድ ክንድ የሆነ ዳርቻ ነበረ፤ የዘበኛ ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ስድስት ክንድ በዚያም በኩል ስድስት ክንድ ነበሩ።
13 ፤ ከአንዱም የዘበኛ ጓዳ ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩን ወርድ ሀያ አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ መዝጊያውና መዝጊያውም ትይዩ ነበረ።
14 ፤ ደጀ ሰላሙንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ፤ በበሩም ደጀ ሰላም ዙሪያ አደባባይ ነበረ።
15 ፤ ከበሩም መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ ደጀ ሰላም መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ።
16 ፤ በዘበኛ ጓዳዎቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ የዓይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩባቸው፤ ደግሞም በደጀ ሰላሙ ውስጥ በዙሪያው መስኮቶች ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።
17 ፤ ወደ ውጭውም አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆም፥ በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ዕቃ ቤቶችና ወለል ነበሩ፤ በወለሉም ላይ ሠላሳ ዕቃ ቤቶች ነበሩ።
18 ፤ ወለሉም በበሮች አጠገብ ነበረ ይህም ታችኛው ወለል እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበረ።
19 ፤ ከታችኛውም በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ወርዱን አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
20 ፤ ወደ ሰሜንም መራኝ፥ እነሆም፥ በውጭው አደባባይ ያለ ወደ ሰሜን የሚመለከት በር ነበረ፤ ርዝመቱንና ወርዱንም ለካ፥
21 ፤ የዘበኛ ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፤ የግንቡ አዕማድና መዛነቢያዎቹም እንደ ፊተኛው በር ልክ ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
22 ፤ መስኮቶቹም መዛነቢያዎቹም የዘንባባ ዛፎቹም ወደ ምሥራቅ እንደሚመለከተው በር ልክ ነበሩ። ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ።
23 ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በሰሜኑና በምሥራቁ በኩል በሌላው በር አንጻር በር ነበረ፤ ከበርም ወደ በር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
24 ፤ ወደ ደቡብም መራኝ፥ እነሆም፥ ወደ ደቡብ የሚመለከት በር ነበረ፤ የግንቡን አዕማድና መዛነቢያዎቹንም እንደዚያው መጠን አድርጎ ለካ።
25 ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ እንደ እነዚያ መስኮቶች የሚመስሉ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
26 ፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፥ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ላይ አንዱ በዚህ አንዱም በዚያ ወገን ሆኖ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።
27 ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በደቡብ በኩል በር ነበረ፤ ከበር እስከ በር ድረስ በደቡብ በኩል መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
28 ፤ በደቡብም በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አገባኝ፤ እንደዚያውም መጠን አድርጎ የደቡብን በር ለካ፤
29 ፤ እንደዚያውም መጠን አድርጎ የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
30 ፤ በዙሪያውም ደጀ ሰላሞች ነበሩ፤ ርዝመታቸውም ሀያ አምስት ክንድ ወርዳቸውም አምስት ክንድ ነበረ።
31 ፤ መዛነቢያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ።
32 ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በምሥራቅ በኩል አገባኝ፥ እንደዚያውም መጠን በሩን ለካ፤
33 ፤ እንደዚያውም መጠን የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፥ ርዝመቱም አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
34 ፤ መዛነቢያዎቹም በስተ ውጭ ወዳለው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
35 ፤ በሰሜንም ወዳለው በር አመጣኝ፥ እንደዚያውም መጠን ለካው፤
36 ፤ የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩበት፥ ርዝመቱም አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
37 ፤ የግንቡም አዕማድ ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
38 ፤ በበሮቹም በግንብ አዕማድ አጠገብ ዕቃ ቤቱና መዝጊያው ነበሩ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያጥቡ ነበር።
39 ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የኃጢአቱንና የበደሉንም መሥዋዕት ያርዱባቸው ዘንድ፥ በበሩ ደጀ ሰላም በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ።
40 ፤ በሰሜን በኩል ባለው በር በስተ ውጭው፥ በመወጣጫው ደረጃዎች አጠገብ፥ በአንድ ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ፥ በሌላውም ወገን በበሩ ደጀ ሰላም በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ።
41 ፤ በበሩ አጠገብ በዚህ ወገን አራት ገበታዎች በዚያም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ መሥዋዕት የሚያርዱባቸው ገበታዎች ስምንት ነበሩ።
42 ፤ ስለሚቃጠለውም መሥዋዕት ርዝመታቸው ክንድ ተኩል ወርዳቸውም ክንድ ተኩል ቁመታቸውም አንድ ክንድ የሆኑ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን የሚያርዱበትን ዕቃ ያኖሩባቸው ዘንድ፥ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ።
43 ፤ በዙሪያውም አንድ ጋት የሆነ ክፈፍ ወደ ውስጥ ተቀልብሶ ነበር፤ በገበታዎቹም ላይ የቍርባኑ ሥጋ ነበረባቸው።
44 ፤ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፥ እነሆም፥ ሁለት ቤቶች ነበሩ፤ አንዱ ወደ ሰሜን በሚመለከት በር አጠገብ ነበረ፥ መግቢያውም ወደ ደቡብ ይመለከት ነበር፤ ሌላውም ወደ ደቡብ በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፥ መግቢያውም ወደ ሰሜን ይመለከት ነበር።
45 ፤ ሰውዬውም። ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው።
46 ፤ ወደ ሰሜንም የሚመለከተው ቤት መሠዊያውን ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው፤ እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል ያገለግሉት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው አለኝ።
47 ፤ አደባባዩንም በአራት ማዕዘኑ ርዝመቱን መቶ ክንድ ወርዱንም መቶ ክንድ አድርጎ ለካ፤ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ።
48 ፤ ወደ ቤቱም ደጀ ሰላም አመጣኝ፥ የደጀ ሰላሙንም የግንብ አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ወርድ አሥራ አራት ክንድ ነበረ፥ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ሦስት ሦስት ክንድ ነበሩ።
49 ፤ የደጀ ሰላሙም ርዝመት ሀያ ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፥ ወደ እርሱም የሚያደርሱ አሥር ደረጃዎች ነበሩ፤ አንድ በዚህ ወገን አንድም በዚያ ወገን ሆነው በመቃኖቹ አጠገብ የግንብ አዕማድ ነበሩ።