ሰቆቃው ኤርምያስ

1 ፤ አሌፍ። ሕዝብ ሞልቶባት የነበረች ከተማ ብቻዋን እንዴት ተቀመጠች! በአሕዛብ መካከል ታላቅ የነበረች እንደ መበለት ሆናለች፤ በአውራጆች መካከል ልዕልት የነበረች ተገዢ ሆናለች።
2 ፤ ቤት። በሌሊት እጅግ ታላቅሳለች፥ እንባዋም በጕንጭዋ ላይ አለ፤ ከውሽሞችዋ ሁሉ የሚያጽናናት የለም፤ ወዳጆችዋ ሁሉ ወነጀሉአት ጠላቶችም ሆኑአት።
3 ፤ ጋሜል። ይሁዳ ስለ መጨነቅና ስለ ባርነት ብዛት ተማረከች፤ በአሕዛብ መካከል ተቀመጠች ዕረፍትም አላገኘችም፤ የሚያስጨንቁአት ሁሉ ተጨንቃ አገኙአት።
4 ፤ ዳሌጥ። ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፤ በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ እርስዋም በምሬት አለች።
5 ፤ ሄ። ስለ ኃጢአትዋ ብዛት እግዚአብሔር አስጨንቆአታልና አስጨናቂዎችዋ ራስ ሆኑ ጠላቶችዋም ተከናወነላቸው፤ ሕፃናቶችዋ በአስጨናቂዎች ፊት ተማርከዋል።
6 ፤ ዋው። ከጽዮን ሴት ልጅ ውበትዋ ሁሉ ወጥቶአል፤ አለቆችዋ ማሰማርያ እንደማያገኙ ዋላዎች ሆኑ፤ ከሚያባርሩአቸው ፊት ተዳክመው ሄዱ።
7 ፤ ዛይ። ኢየሩሳሌም በጭንቀትዋና በመከራዋ ወራት ከጥንት ጀምሮ የነበረላትን የከበረን ነገር ሁሉ አሰበች፤ ሕዝብዋ በአስጨናቂዎች እጅ በወደቀ ጊዜ የሚረዳትም በሌላት ጊዜ፥ አስጨናቂዎች አዩአት በመፍረስዋም ሳቁ።
8 ፤ ሔት። ኢየሩሳሌም እጅግ ኃጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህ ረክሳለች፤ ያከብሩአት የነበሩ ሁሉ ኀፍረተ ሥጋዋን አይተዋታልና አቃለሉአት፤ እርስዋም እየጮኸች ታለቅሳለች ወደ ኋላም ዘወር አለች።
9 ፤ ጤት። አደፍዋ በልብስዋ ዘርፍ ነበረ፤ ፍጻሜዋን አላሰበችም፤ ስለዚህ በድንቅ ተዋርዳለች፥ የሚያጽናናትም የለም፤ አቤቱ፥ ጠላት ከፍ ከፍ ብሎአልና መከራዬን ተመልከት።
10 ፤ ዮድ። አስጨናቂው በከበረ ነገርዋ ሁሉ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ ያዘዝሃቸው አሕዛብ ወደ መቅደስዋ ሲገቡ አይታለችና።
11 ፤ ካፍ። ሕዝብዋ ሁሉ እየጮኹ ያለቅሳሉ እንጀራም ይፈልጋሉ፤ ሰውነታቸውን ለማበርታት የከበረ ሀብታቸውን ስለ መብል ሰጥተዋል፤ አቤቱ፥ ተጐሳቍያለሁና እይ፥ ተመልከትም።
12 ፤ ላሜድ። እናንተ መንገድ አላፊዎች ሁሉ፥ በእናንተ ዘንድ ምንም የለምን? እግዚአብሔር በጽኑ ቍጣው ቀን እኔን እንዳስጨነቀበት በእኔ ላይ እንደ ተደረገው እንደ እኔ መከራ የሚመስል መከራ እንዳለ ተመልከቱ፥ እዩ።
13 ፤ ሜም። ከላይ እሳትን ወደ አጥንቴ ሰደደ በረታችበትም፤ ለእግሬ ወጥመድ ዘረጋ ወደ ኋላም መለሰኝ፥ አጠፋኝም ቀኑንም ሁሉ አደከመኝ።
14 ፤ ኖን። የኃጢአቶቼ ቀንበር በእጁ ተይዛለች፤ ታስረው በአንገቴ ላይ ወጥተዋል፤ ጕልበቴን አደከመ። ጌታ በፊታቸው እቆም ዘንድ በማልችላቸው እጅ አሳልፎ ሰጠኝ።
15 ፤ ሳምኬት። ጌታ ኃያላኖቼን ሁሉ ከውስጤ አስወገዳቸው፤ ጕልማሶቼን ያደቅቅ ዘንድ ጉባኤን ጠራብኝ፤ ጌታ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በመጥመቂያ እንደሚረገጥ አድርጎ ረገጣት።
16 ፤ ዔ። የሚያጽናናኝ ነፍሴንም የሚያበረታት ከእኔ ርቆአልና ስለዚህ አለቅሳለሁ፤ ዓይኔ፥ ዓይኔ ውኃ ያፈስሳል። ጠላት በርትቶአልና ልጆቼ ጠፍተዋል።
17 ፤ ፌ። ጽዮን እጅዋን ዘረጋች፤ የሚያጽናናት የለም፤ እግዚአብሔር በያዕቆብ ዙሪያ ያሉትን እንዲያስጨንቁት አዘዘ፤ ኢየሩሳሌም በመካከላቸው እንደ ርኩስ ነገር ሆናለች።
18 ፤ ጻዴ። በአፉ ነገር ላይ ዓመፅ አድርጌአለሁና እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ እባካችሁ፥ ስሙ መከራዬንም ተመልከቱ፤ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ ተማርከው ሄዱ።
19 ፤ ቆፍ። ውሽሞቼን ጠራሁ እነርሱም አታለሉኝ፤ ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ ሰውነታቸውን ያበረቱ ዘንድ መብል ሲፈልጉ በከተማ ውስጥ ሞቱ።
20 ፤ ሬስ። አቤቱ፥ ተጨንቄአለሁና፥ አንጀቴም ታውኮብኛልና ተመልከት፤ ዓመፃን ፈጽሞ አድርጌአለሁና ልቤ በውስጤ ተገላበጠብኝ፤ በሜዳ ሰይፍ ልጆቼን አጠፋ በቤትም ሞት አለ።
21 ፤ ሳን። እኔ እየጮኽሁ እንደማለቅስ ሰምተዋል፤ የሚያጽናናኝ የለም፤ ጠላቶቼ ሁሉ ስለ መከራዬ ሰምተዋል፤ አንተ አድርገኸዋልና ደስ አላቸው፤ ስለ እርሱ የተናገርኸውን ቀን ታመጣለህ እነርሱም እንደ እኔ ይሆናሉ።
22 ፤ ታው። ልቅሶዬ እጅግ ነውና፥ ልቤም ደክሞአልና ክፋታቸው ሁሉ ወደ ፊትህ ይድረስ፥ ስለ ኃጢአቴ ሁሉ እንዳደረግህብኝ አድርግባቸው።