መጽሐፈ ሳሙኤል ካል

1 ፤ እንዲህም ሆነ፥ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመልሶ በጺቅላግ ሁለት ቀን ያህል ተቀመጠ።
2 ፤ በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሳኦል ሰፈር አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፤ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ።
3 ፤ ዳዊትም። ከወዴት መጣህ? አለው እርሱም። ከእስራኤል ሰፈር ኰብልዬ መጣሁ አለው።
4 ፤ ዳዊትም። ነገሩ እንደ ምን ሆነ? እስኪ ንገረኝ አለው። እርሱም መልሶ። ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፥ ከሕዝቡ ብዙው ወደቁ ሞቱም፤ ሳኦልና ልጁም ዮናታን ደግሞ ሞተዋል አለ።
5 ፤ ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ። ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ በምን ታውቃለህ? አለው።
6 ፤ ወሬኛውም ጕልማሳ አለ። በድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ መጣሁ፥ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩን ተመርኵዞ ቆሞ ነበር፤ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት።
7 ፤ ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁ።
8 ፤ እርሱም። አንተ ማን ነህ? አለኝ፤ እኔም። አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት።
9 ፤ እርሱም። ሰውነቴ ዝሎአልና፥ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያው ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ።
10 ፤ እኔም ከወደቀ በኋላ አለ መዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፥ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት።
11 ፤ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ይዘው ቀደዱ።
12 ፤ በሰይፍም ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ለእግዚአብሔርም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፥ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ።
13 ፤ ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ። አንተ ከወዴት ነህ? አለው፤ እርሱም። እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ ብሎ መለሰለት።
14 ፤ ዳዊትም። እግዚአብሔር የቀባውን ለመግደል እጅህን ስትዘረጋ ለምን አልፈራህም? አለው።
15 ፤ ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ። ወደ እርሱ ቅረብና ውደቅበት አለው። እርሱም መታው፥ ሞተም።
16 ፤ ዳዊትም። እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን አለው።
17 ፤ ዳዊትም ስለ ሳኦልና ሰለ ልጁ ስለ ዮናታን ይህን የኀዘን ቅኔ ተቀኘ፥
18 ፤ የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ፥ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል።
19 ፤ የእስራኤል ክብር በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞተ፤ ኃያላን እንዴት ወደቁ!
20 ፤ የፍልስጥኤማውያን ቈነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፥ የቈላፋንም ቈነጃጅት እልል እንዳይሉ፥ በጌት ውስጥ አታውሩ፤ በአስቀሎናም አደባባይ የምስራች አትበሉ።
21 ፤ እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፥ የሳኦል ጋሻ በዘይት እንዳልተቀባ፥ የኃያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፥ ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ።
22 ፤ ከሞቱት ደምና ከኃያላን ስብ የዮናታን ቀስት አልተመለሰችም፥ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰም።
23 ፤ ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፤ በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፤ ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፤ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።
24 ፤ የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፥ ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥ በወርቀዘቦም ላስጌጣችሁ ለሳኦል አልቅሱለት።
25 ፤ ኃያላንም በሰልፍ ውስጥ እንዴት ወደቁ! ዮናታንም በኮረብቶችህ ላይ ወድቆአል።
26 ፤ ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበረ፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ።
27 ፤ ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ!