ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 29

1 ፤ በአሥረኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፥ በእርሱና በግብጽ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፥
3 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በወንዞች መካከል የምትተኛና። ወንዙ የእኔ ነው ለራሴም ሠርቼዋለሁ የምትል ታላቅ አዞ፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ።
4 ፤ በመንጋጋህ መቃጥን አገባብሃለሁ፥ የወንዞችህንም ዓሦች ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ፤ ከወንዞችህም መካከል አወጣሃለሁ፥ የወንዞችህም ዓሦች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ ይጣበቃሉ።
5 ፤ አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፥ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጂ አትከማችም አትሰበሰብም መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሰጥቼሃለሁ።
6 ፤ በግብጽም የሚኖሩ ሁሉ ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሆነዋልና እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7 ፤ በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ ጫንቃቸውንም ሁሉ አቈሰልህ፤ በተደገፉብህም ጊዜ ተሰበርህ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ።
8 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ።
9 ፤ የግብጽም ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ አንተ። ወንዙ የእኔ ነው የሠራሁትም እኔ ነኝ ብለሃልና።
10 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፥ የግብጽንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ።
11 ፤ የሰው እግር አያልፍባትም የእንስሳም ኮቴ አያልፍባትም፥ እስከ አርባ ዓመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም።
12 ፤ ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብጽን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ፥ በፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ አርባ ዓመደ ፈርሰው ይቀመጣሉ፤ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናቸዋለሁ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ።
13 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአርባ ዓመት በኋላ ግብጻውያንን ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባለሁ፤
14 ፤ የግብጽንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ወደ ተወለዱባትም ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ።
15 ፤ ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ ይልቅ የተዋረደች ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲያ በአሕዛብ ላይ ከፍ አትልም፤ በአሕዛብም ላይ እንዳይገዙ አሳንሳቸዋለሁ።
16 ፤ የእስራኤል ቤት እነርሱን በተከተሉ ጊዜ እርስዋ በደልን ታሳስባለች፥ ከእንግዲህም ወዲያ መታመኛ አትሆንላቸውም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
17 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በሀያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን በጢሮስ ላይ ጽኑ አገልግሎት አስገለገለ፤ ራስ ሁሉ የተላጨ ጫንቃም ሁሉ የተላጠ ሆኖአል፤ ነገር ግን በላይዋ ስላገለገለው አገልግሎት እርሱና ሠራዊቱ ደመወዝ ከጢሮስ አልተቀበሉም።
19 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የግብጽን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፥ ብዛትዋንም ይወስዳል ምርኮዋንም ይማርካል ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል።
20 ፤ ስለ እኔ ሠርተዋልና ስለ አገልግሎቱ ደመወዝ የግብጽን ምድር ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21 ፤ በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፥ በመካከላቸውም ለአንተ የተከፈተ አፍን እሰጣለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።