ትንቢተ ናሆም

1 ፤ ስለ ነነዌ የተነገረ ሸክም፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው።
2 ፤ እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ተበቃይና መዓትን የተሞላ ነው፤ እግዚአብሔር ተቃዋሚዎቹን ይበቀላል፥ ለጠላቶቹም ቍጣውን ይጠብቃል።
3 ፤ እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም። ንጹሕ ነህ አይልም፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።
4 ፤ ባሕሩንም ይገሥጻታል፥ ያደርቃትማል፥ ወንዞችንም ሁሉ ያደርቃል፤ ባሳንና ቀርሜሎስም ላልተዋል፥ የሊባኖስም አበባ ጠውልጎአል።
5 ፤ ተራሮችም ከእርሱ የተነሣ ታወኩ፥ ኮረብቶችም ቀለጡ፤ ምድርና ዓለም የሚኖሩበትም ሁሉ ከፊቱ ተናወጡ።
6 ፤ በቍጣው ፊት የሚቆም ማን ነው? የቍጣውንም ትኵሳት ማን ይታገሣል? መዓቱ እንደ እሳት ይፈስሳል፥ ከእርሱም የተነሣ ዓለቶች ተሰነጠቁ።
7 ፤ እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል።
8 ፤ ስፍራዋን ግን በሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ፈጽሞ ያጠፋታል፥ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።
9 ፤ በእግዚአብሔር ላይ የምታስቡት ምንድር ነው? እርሱ ፈጽሞ ያጠፋል፥ መከራም ሁለተኛ አይነሣም።
10 ፤ እርስ በእርሳቸው እንደ ተመሰቃቅለ እሾህ ቢሆኑ፥ በመጠጣቸውም ቢሰክሩ እንደ ደረቅ ገለባ ፈጽመው ይጠፋሉ።
11 ፤ በእግዚአብሔር ላይ በክፉ የሚያስብ፥ ክፋትን የሚመክር፥ ከአንተ ዘንድ ወጥቶአል።
12 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኃይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑ እንዲሁ ይቈረጣሉ፥ እርሱም ያልቃል። እኔም አስጨንቄሃለሁ፥ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አላስጨንቅህም።
13 ፤ አሁንም ቀንበሩን ከአንተ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ።
14 ፤ እግዚአብሔርም ከስምህ ማንም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይዘራ ስለ አንተ አዝዞአል፤ ከአምላኮችህ ቤት የተቀረጸውንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል አጠፋለሁ፤ አንተም የተጠቃህ ነህና መቃብርህን እምሳለሁ።
15 ፤ እነሆ፥ የምስራችን የሚያመጣ ሰላምንም የሚያወራ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው! ይሁዳ ሆይ፥ አጥፊው ፈጽሞ ጠፍቶአልና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በአንተ ዘንድ አያልፍምና ዓመት በዓሎችህን አድርግ፥ ስእለቶችህን ክፈል።