ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 25

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ አሞን ልጆች አቅንተህ ትንቢት ተናገርባቸው።
3 ፤ ለአሞንም ልጆች እንዲህ በል። የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መቅደሴ በረከሰ ጊዜ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ የይሁዳም ቤት በተማረኩ ጊዜ ስለ እነርሱ እሰይ ብለሃልና
4 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ርስት አድርጌ ለምሥራቅ ልጆች አሳልፌ አሰጥሃለሁ፥ እነርሱም በአንተ ውስጥ ይሰፍራሉ፥ ማደሪያዎቻቸውንም በአንተ ዘንድ ይሠራሉ፤ ፍሬህን ይበላሉ ወተትህንም ይጠጣሉ፤
5 ፤ የአሞንን ከተማ ለግመሎች ማሰማርያ፥ የአሞንንም ልጆች ለመንጋ መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
6 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በእጅህ አጨብጭበሃልና፥ በእግርህም አሸብሽበሃልና፥ በእስራኤልም ምድር ላይ በነፍስህ ንቀት ሁሉ ደስ ብሎሃልና
7 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን ዘርግቼብሃለህ፥ ለአሕዛብም አስበዘብዝሃለሁ፥ ከአሕዛብም ለይቼ እቈርጥሃለሁ፥ ከአገሮችም አጠፋሃለሁ እፈጅህማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
8 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሞዓብና ሴይር። እነሆ፥ የይሁዳ ቤት እንደ አሕዛብ ሁሉ ነው ብለዋልና
9 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሞዓብን ጫንቃ ከከተሞቹ፥ በዳርቻው ካሉት የምድሩ ትምክሕት ከሆኑት ከተሞቹ፥ ከቤትየሺሞት፥ ከበኣልሜዎን፥
10 ፤ ከቂርያታይም፥ ከአሞን ልጆች ጋር ለምሥራቅ ልጆች እከፍታለሁ። የአሞን ልጆች በአሕዛብ መካከል ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰቡ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።
11 ፤ በሞዓብም ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
12 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኤዶምያስ በይሁዳ ቤት ላይ በቀል አድርጎአልና፥ ቂም ይዞአልና፥ ብድራትንም አስከፍሎአልና
13 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ ከቴማንም ጀምሮ ባድማ አደርጋታለሁ፥ እስከ ድዳንም ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ።
14 ፤ በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምያስን እበቀላለሁ፤ እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴም መጠን በኤዶምያስ ያደርጋሉ፤ በቀሌንም ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ፍልስጥኤማውያን በቀልን አድርገዋልና፥ በዘወትርም ጠላትነት ያጠፉ ዘንድ በነፍሳቸው ንቀት ተበቅለዋልና
16 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እጄን በፍልስጥኤማውያን ላይ እዘረጋለሁ፥ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፥ የባሕሩንም ዳር ቅሬታ አጠፋለሁ።
17 ፤ በመዓት መቅሠፍትም ታላቅ በቀል አደርግባቸዋለሁ፤ በቀሌንም በላያቸው ባደረግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።