ትንቢተ ዕንባቆም

1 ፤ ነቢዩ ዕንባቆም ያየው ሸክም ይህ ነው።
2 ፤ አቤቱ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም።
3 ፤ በደልንስ ስለ ምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብና ክርክር ይነሣሉ።
4 ፤ ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፥ ፍርድም ድል ነሥቶ አይወጣም፤ ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና፤ ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል።
5 ፤ እናንተ የምትንቁ ሆይ፥ አንድ ቢተርክላችሁ ስንኳ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁና እዩ፥ ተመልከቱ፥ ተደነቁ።
6 ፤ እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ።
7 ፤ እነርሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል።
8 ፤ ፈረሶቻቸውም ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፥ ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው፤ ፈረሰኞቻቸውም ይንሳፈፋሉ፥ ከሩቅም ይመጣሉ፥ ለመብልም እንደሚቸኵል ንስር ይበርራሉ።
9 ፤ ሁሉም ለግፍ ሥራ ይመጣሉ፥ ፊታቸውንም እንደ ምሥራቅ ነፋስ ያቀናሉ፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ።
10 ፤ በነገሥታት ላይ ያላግጣሉ፥ መሳፍንትም ዋዛ ሆነውላቸዋል፤ በምሽጉ ሁሉ ይስቃሉ፥ አፈሩንም ከምረው ይወስዱታል።
11 ፤ የዚያን ጊዜም እንደ ነፋስ አልፎ ይሄዳል፥ ይበድልማል፤ ኃይሉንም አምላክ ያደርገዋል።
12 ፤ አቤቱ፥ የተቀደስህ አምላኬ ሆይ፥ አንተ ከዘላለም ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፤ አቤቱ፥ ለፍርድ ሠርተኸዋል፥ ለተግሣጽም አድርገኸዋል።
13 ፤ ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፥ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም፤ አታላዮችንስ ለምን ትመለከታለህ? ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለ ምን ዝም ትላለህ?
14 ፤ ሰዎችንም እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ አለቃም እንደሌላቸው ተንቀሳቃሾች ለምን ታደርጋቸዋለህ?
15 ፤ ሁሉን በመቃጥን ያወጣል፥ በመረቡም ይይዛቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፤ ስለዚህ ደስ እያለው እልል ይላል።
16 ፤ እድል ፈንታው በእነርሱ ሰብታለችና፥ መብሉም በዝቶአልና ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል።
17 ፤ ስለዚህ መረቡን ይጥላልን? አሕዛብንም ዘወትር ይገድል ዘንድ አይራራምን?