ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 26

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ። እሰይ፥ የአሕዛብ በር የነበረች ተሰብራለች ወደ እኔም ተመልሳለች፤ እርስዋ ፈርሳለችና እኔ እሞላለሁ ብላለችና
3 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጢሮስ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ባሕርም ሞገድዋን እንደምታወጣ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን አወጣብሻለሁ።
4 ፤ የጢሮስንም ቅጥሮች ያጠፋሉ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ ትቢያዋንም ከእርስዋ እፍቃለሁ፥ የተራቈተ ድንጋይም አደርጋታለሁ።
5 ፤ በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአሕዛብም ብዝበዛ ትሆናለች።
6 ፤ በሜዳ ያሉትም ሴቶች ልጆችዋ በሰይፍ ይገደላሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ከፈረሶችና ከሰረገሎች ከፈረሰኞችም ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብ ጋር በጢሮስ ላይ አመጣለሁ።
8 ፤ በሜዳ ያሉትን ሴቶች ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፥ አምባም ይሠራብሻል አፈርንም ይደለድልብሻል ጋሻም ያነሣብሻል።
9 ፤ ማፍረሻውን በቅጥርሽ ላይ ያደርጋል፥ ግንቦችሽንም በምሳር ያፈርሳል።
10 ፤ ከፈረሶቹም ብዛት የተነሣ ትቢያቸው ይከድንሻል፤ ሰዎችም በተናደች ቅጥር ወደ ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ ሲገባ፥ ከፈረሰኞችና ከመንኰራኵሮች ከሰረገሎችም ድምፅ የተነሣ ቅጥርሽ ትናወጣለች።
11 ፤ በፈረሶቹ ኮቴ ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረመርማል፥ ሕዝብሽንም በሰይፍ ይገድላል፥ የብርታትሽም ሐውልት ወደ ምድር ይወድቃል።
12 ፤ ብልጥግናሽንም ይማርካሉ፥ ሸቀጥሽንም ይበዘብዛሉ፤ ቅጥርሽንም ያፈርሳሉ፥ ተድላ የምታደርጊባቸውን ቤቶችሽን ያጠፋሉ፤ ድንጋይሽንና እንጨትሽን መሬትሽንም በባሕር ውስጥ ይጥላሉ።
13 ፤ የዘፋኞችሽንም ብዛት ዝም አሰኛለሁ፤ የመሰንቆሽም ድምፅ ከዚያ ወዲያ አይሰማም።
14 ፤ የተራቈተ ድንጋይ አደርግሻለሁ የመረብም ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አትሠሪም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
15 ፤ ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላታል። የተወጉት ባንቋረሩ ጊዜ፥ በውስጥሽ እልቂት በሆነ ጊዜ፥ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች ይነዋወጡ የለምን?
16 ፤ የባሕርም አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ያወጣሉ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፤ መንቀጥቀጥን ለብሰው በመሬት ላይ ይቀመጣሉ፥ ሁልጊዜም ይንቀጠቀጣሉ በአንቺም ይደነቃሉ።
17 ፤ በአንቺም ላይ ሙሾ ያሞሻሉ፥ እንዲህም ይሉሻል። በባሕር የተቀመጥሽ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ የከበርሽ ከተማ ሆይ፥ እንዴት ጠፋሽ!
18 ፤ አሁን በውድቀትሽ ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፥ በባሕርም ውስጥ ያለ ደሴቶች ከመጥፋትሽ የተነሣ ይደነግጣሉ።
19 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰው እንደሌለባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ቀላዩንም ባወጣሁብሽ ጊዜ ብዙ ውኆችም በከደኑሽ ጊዜ፥
20 ፤ የቀድሞ ሕዝብ ወዳሉበት ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋር አወርድሻለሁ፤ የሚኖርብሽም እንዳይገኝ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ቀድሞ በፈረሰችው ስፍራ፥ በታችኛይቱ ምድር አኖርሻለሁ፤ ጌጥሽንም በሕያዋን ምድር አላኖርም።
21 ፤ ለድንጋጤ አደርግሻለሁ እንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊአለሽ ለዘላለምም አትገኚም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።