ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 20

1 ፤ አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር ሄደ፥ በቃዴስና በሱር መካከልም ተቀመጠ፤ በጌራራም በእንግድነት ተቀመጠ።
2 ፤ አብርሃምም ሚስቱን ሣራን። እኅቴ ናት አለ፤ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክም ላከና ሣራን ወሰዳት።
3 ፤ እግዚአብሔርም ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፥ እንዲህም አለው። እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ምውት ነህ፤ እርስዋ ባለ ባል ናትና።
4 ፤ አቢሜሌክ ግን አልቀረባትም ነበር፤ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ ጻድቁን ሕዝብ ደግሞ ታጠፋለህን?
5 ፤ እኅቴ ናት ያለኝ እርሱ አይደለምን? እርስዋም ደግሞ ራስዋ። ወንድሜ ነው አለች፤ በልቤ ቅንነትና በእጄ ንጹሕነት ይህንን አደረግሁ።
6 ፤ እግዚአብሔርም በሕልም አለው። ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ አወቅሁ፥ እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ፤ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውሁም።
7 ፤ አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ።
8 ፤ አቢሜሌክም በነገታው ማለደ፥ ባሪያዎቹንም ሁሉ ጠራ፥ ይህንንም ነገር ሁሉ በጆሮአቸው ተናገረ፤ ሰዎቹም እጅግ ፈሩ።
9 ፤ አቢሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምንስ ክፉ ሠራሁብህ? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ትልቅ ኃጢአት አውርደሃልና፤ የማይገባ ሥራ በእኔ ሠራህብኝ።
10 ፤ አቢሜሌክም አብርሃምን አለው። ይህን ማድረግህ ምን አይተህ ነው?
11 ፤ አብርሃምም አለ። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን መፍራት በእውነት እንደሌለ፥ ለሚስቴም ሲሉ እንደሚገድሉኝ ስላሰብሁ ነው።
12 ፤ እርስዋም ደግሞ በእውነት እኅቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ አይደለችም እንጂ የአባቴ ልጅ ናት፤ ለእኔም ሚስት ሆነች።
13 ፤ እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ አልኋት። በገባንበት አገር ሁሉ ለእኔ የምታደርጊው ወሮታ ይህ ነው። ወንድሜ ነው ብለሽ ስለ እኔ ተናገሪ።
14 ፤ አቢሜሌክም በጎችንና ላሞችን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችን አመጣ፥ ለአብርሃምም ሰጠው፥ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት።
15 ፤ አቢሜሌክም። እነሆ፥ ምድሬ በፊትህ ናት፤ በወደድኸው ተቀመጥ አለ።
16 ፤ ሣራንም አላት። እነሆ፥ ለወንድምሽ ሺህ ሚዛን ብር ሰጠሁት፤ ያም እነሆ ከአንቺ ጋር ባሉት ሁሉ ፊት የዓይኖች መሸፈኛ ይሁንሽ፤ ጽድቅሽ ለሰዎች ሁሉ ተገልጦአልና።
17 ፤ አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን ሚስቱንም ባሪያዎቹንም ፈወሳቸው፥ እነርሱም ወለዱ፤
18 ፤ እግዚአብሔር በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቢሜሌክ ቤት ማኅፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና። a