ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 27

1 ፤ ይስሐቅ ሸምግሎ ዓይኖቹ ከማየት በፈዘዙ ጊዜ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ። ልጄ ሆይ አለው፤ እርሱም። እነሆ አለሁ አለው።
2 ፤ እርሱም አለው። እነሆ እኔ አረጀሁ፥ የምሞትበትን ቀን አላውቅም።
3 ፤ አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፥ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፥ አደንም አድንልኝ፤
4 ፤ ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ የጣፈጠ መብል እኔ እንደምወደው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ።
5 ፤ ርብቃም ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው ሲነግር ትሰማ ነበር። ዔሳውም አደን አድኖ ሊያመጣ ወደ ምድረ በዳ ሄደ።
6 ፤ ርብቃም ልጅዋን ያዕቆብን እንዲህ አለችው። እነሆ፥ አባትህ ለወንድምህ ለዔሳው።
7 ፤ አደን አድነህ አምጣልኝ፥ ሳልሞትም በልቼ በእግዚአብሔር ፊት እንድባርክህ የጣፈጠ መብል አድርግልኝ ብሎ ሲነግረው ሰማሁ።
8 ፤ አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እኔ በማዝዝህ ነገር ስማኝ፤
9 ፤ ወደ መንጋ ሄደህ ሁለት መልካካም ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እነርሱንም ጣፋጭ መብል ለአባትህ እንደሚወደው አደርጋለሁ፤
10 ፤ ለአባትህም፥ ሳይሞት እንዲባርክህ፥ ይበላ ዘንድ ታገባለታለህ።
11 ፤ ያዕቆብም ርብቃን እናቱን አላት። እነሆ ዔሳው ወንድሜ ጠጕራም ሰው ነው፥ እኔ ግን ለስላሳ ነኝ፤
12 ፤ ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደሚዘብት እሆናለሁ፤ መርገምንም በላዬ አመጣለሁ፥ በረከትን አይደለም።
13 ፤ እናቱም አለችው። ልጄ ሆይ፥ መርገምህ በእኔ ላይ ይሁን፤ ቃሌን ብቻ ስማኝ፤ ሂድና አምጣልኝ።
14 ፤ ሄዶም አመጣ፥ ለእናቱም ሰጣት፤ እናቱም የጣፈጠውን መብል አባቱ እንደሚወደው አደረገች።
15 ፤ ርብቃም ከእርስዋ ዘንድ በቤት የነበረችውን የታላቁን ልጅዋን የዔሳውን መልካሙን ልብስ አመጣች፥ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አለበሰችው፤
16 ፤ የጠቦቶችንም ለምድ በእጆቹና በለስላሳው አንገቱ ላይ አደረገች፤
17 ፤ የሠራችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራውን ለልጅዋ ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው።
18 ፤ ወደ አባቱም ገብቶ። አባቴ ሆይ አለው እርሱም። እነሆኝ፤ ልጄ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አለ።
19 ፤ ያዕቆብም አባቱን አለው። የበኵር ልጅህ እኔ ዔሳው ነኝ፤ እንዳዘዝኽኝ አደረግሁ፤ ነፍስህ ትባርከኝ ዘንድ ቀና በልና ተቀመጥ፥ ካደንሁትም ብላ።
20 ፤ ይስሐቅም ልጁን። ልጄ ሆይ፥ እንዴት ፈጥነህ አገኘኸው? አለው። እርሱም። እግዚአብሔር አምላክህ ወደ እኔ ስለ አቀረበው ነው አለ።
21 ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ልጄ ዔሳው እንደ ሆንህ ወይም እንዳልሆንህ እዳስስህ ዘንድ ቅረበኝ አለው።
22 ፤ ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ፤ ዳሰሰውም፥ እንዲህም። ይህ ድምፅ የያዕቆብም ድምፅ ነው፥ እጆች ግን የዔሳው እጆች ናቸው አለው።
23 ፤ እርሱም አላወቀውም ነበር፤ እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ነበሩና፤ ስለዚህም ባረከው።
24 ፤ አለውም። አንተ ልጄ ዔሳው ነህን? እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
25 ፤ እርሱም። ከልጄ አደን እንድበላና ነፍሴ እንድትባርክህ አቅርብልኝ አለ። አቀረበለትም፥ በላም፤ የወይን ጠጅ አመጣለት፥ እርሱም ጠጣ።
26 ፤ አባቱ ይስሐቅም። ልጄ ሆይ፥ ወደ እኔ ቅረብ ሳመኝም አለው።
27 ፤ ወደ እርሱም ቀረበ፥ ሳመውም፤ የልብሱንም ሽታ አሸተተ፥ ባረከውም፥ እንዲህም አለ። የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው እርሻ ሽታ ነው፤
28 ፤ እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል ከምድርም ስብ የእህልንም የወይንንም ብዛት ይስጥህ፤
29 ፤ አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ፤ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።
30 ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ባርኮ ከፈጸመ በኋላ፥ ያዕቆብም ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት ከወጣ በኋላ፥ ወዲያው በዚያው ጊዜ ዔሳው ከአደኑ መጥቶ ገባ።
31 ፤ እርሱም ደግሞ ጣፋጭ መብል አዘጋጀ፥ ለአባቱም አገባ፤ አባቱንም። አባቴ ይነሣ፥ ነፍስህም ትባርከኝ ዘንድ ከልጁ አደን ይብላ አለው።
32 ፤ አባቱ ይስሐቅም። አንተ ማን ነህ? አለው፤ እርሱም። እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ አለው።
33 ፤ ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ እንዲህም አለ። ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣ ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ ባረክሁትም፤ እርሱም የተባረከ ሆኖ ይኖራል።
34 ፤ ዔሳውም የአባቱን ቃል በሰማ ጊዜ ታላቅ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ፥ አባቱንም። አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ አለው።
35 ፤ እርሱም። ወንድምህ በተንኮል ገብቶ በረከትህን ወሰደብህ አለ።
36 ፤ እርሱም አለ። በእውነት ስሙ ያዕቆብ ተባለ፥ ሁለት ጊዜ አሰናክሎኛልና፤ ብኵርናዬን ወሰደ፥ አሁንም እነሆ በረከቴን ወሰደ። ደግሞም። ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን? አለ።
37 ፤ ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው። እነሆ፥ ጌታህ አደረግሁት፥ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች ይሆኑ ዘንድ ሰጠሁት፥ በእህልም በወይንም አበረታሁት፤ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግ?
38 ፤ ዔሳውም አባቱን አለው። አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ። ዔሳውም ቃሉን አንሥቶ አለቀሰ።
39 ፤ አባቱ ይስሐቅም መለሰ አለውም። እነሆ፥ መኖሪያህ ከምድር ስብ ከላይ ከሚገኝ ከሰማይም ጠል ይሆናል፤
40 ፤ በሰይፍህም ትኖራለህ፥ ለወንድምህም ትገዛለህ፤ ነገር ግን በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለህ።
41 ፤ ዔሳውም አባቱ ስለ ባረከው በያዕቆብ ቂም ያዘበት፤ ዔሳውም በልቡ አለ። ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቦአል፥ ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ።
42 ፤ ለርብቃም ይህ የታላቁ ልጅዋ የዔሳው ቃል ደረሰላት፤ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አስጠርታ አስመጣችው፥ አለችውም። እነሆ፥ ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ይፈቅዳል።
43 ፤ አሁንም ልጄ ሆይ ቃሌን ስማ፤ ተነሣና ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ፤
44 ፤ በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ፥ የወንድምህ ቍጣ እስኪበርድ ድረስ፤
45 ፤ የወንድምህ ቍጣ ከአንተ እስኪመለስ ድረስ፥ ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ፤ ከዚያም ልኬ አስመጣሃለሁ፤ በአንድ ቀን ሁለታችሁን ለምን አጣለሁ?
46 ፤ ርብቃም ይስሐቅን አለችው። ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?