ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 31

1 ፤ ያዕቆብም የላባ ልጆች ያሉትን ነገር። ያዕቆብ ለአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፤ ይህንም ሁሉ ክብር ከአባታችን ከብት አገኘ ሲሉ ሰማ።
2 ፤ ያዕቆብም የላባን ፊት አየ፥ እነሆም ከእርሱ ጋር እንደ ዱሮው አልሆነም።
3 ፤ እግዚአብሔርም ያዕቆብን። ወደ አባትህ ምድር ወደ ዘመዶችህም ተመለስ፤ ከአንተም ጋር እሆናለሁ አለው።
4 ፤ ያዕቆብም ልኮ ራሔልንና ልያን ወደ በጎቹ ስፍራ ወደ ሜዳ ጠራቸው፥
5 ፤ እንዲህም አላቸው። የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደ ዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው።
6 ፤ እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ።
7 ፤ አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉ ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም።
8 ፤ ደመወዝህ ዝንጕርጕሮች ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ፤ ሽመልመሌ መሳዮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮችን ወለዱ።
9 ፤ እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ።
10 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በጎቹ በጎመጁ ጊዜ ዓይኔን አንሥቼ በሕልም አየሁ፤ እነሆም፥ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ነበሩ።
11 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት።
12 ፤ እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና።
13 ፤ ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።
14 ፤ ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት። በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻና ርስት በውኑ ቀርቶልናልን?
15 ፤ እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና።
16 ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ይህ ሁሉ ሀብት ለእኛና ለልጆቻችን ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ።
17 ፤ ያዕቆብም ተነሣ፥ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤
18 ፤ መንጎቹንም ሁሉ፥ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ፥ በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ።
19 ፤ ላባ ግን በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባትዋን ተራፊም ሰረቀች።
20 ፤ ያዕቆብም የሶርያውን ሰው ላባን ከድቶ ኮበለለ፥ መኮብለሉንም፥ አልነገረውም።
21 ፤ እርሱም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፤ ተነሥቶም ወንዙን ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ገለዓድ ተራራ አቀና።
22 ፤ በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ተነገረው።
23 ፤ ከወንድሞቹም ጋር ሆኖ የሰባት ቀን መንገድ ያህል ተከተለው፥ በገለዓድ ተራራም ላይ ደረሰበት።
24 ፤ እግዚአብሔርም ወደ ሶርያው ሰው ወደ ላባ በሌሊት ሕልም መጥቶ። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ አለው።
25 ፤ ላባም ደረሰበት፤ ያዕቆብም ድንኳኑን በተራራው ተክሎ ነበር፤ ላባም ከወንድሞቹ ጋር በገለዓድ ተራራ ድንኳኑን ተከለ።
26 ፤ ላባም ያዕቆብን አለው። ለምን እንዲህ አደረግህ? ከእኔ ከድተህ ኮበለልህ፥ ልጆቼንም በሰይፍ እንደ ተማረኩ ዓይነት ነዳሃቸው።
27 ፤ ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኮበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም?
28 ፤ ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቼን እንድስም ስለ ምን አልፈቀድህልኝም? ይህንም በስንፍና አደረግህ።
29 ፤ ክፉ አደርግባችሁ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፤ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ ብሎ ነገረኝ።
30 ፤ አሁንም የአባትህን ቤት ከናፈቅህ ሂድ፤ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ?
31 ፤ ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። ልጆችህን ከእኔ የምትቀማኝ ስለመሰለኝና ስለፈራሁ ይህን አደረግሁ።
32 ፤ አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፤ የአንተ የሆነውም በእኔ ዘንድ ይገኝ እንደ ሆነ በወንድሞቻችን ፊት ፈልግ፥ ለአንተም ውሰደው አለ። ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው ያዕቆብ አያውቅም ነበርና።