ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 13

1 ፤ አብራምም ከግብፅ ወጣ፤ እርሱና ሚስቱ ለእርሱ የነበረውም ሁሉ ሎጥም ከእርሱ ጋር ወደ አዜብ ወጡ።
2 ፤ አብራምም በከብት በብርና በወርቅ እጅግ በለጠገ።
3 ፤ ከአዜብ ባደረገው በጕዞውም ወደ ቤቴል በኩል ሄደ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳን ተክሎበት የነበረው ነው፤
4 ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ መሠውያ የሠራበት ነው፤ በዚያም አብራም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ።
5 ፤ ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው።
6 ፤ በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም የነበራቸው እጅግ ነበረና በአንድነት ሊቀመጡ አልቻሉም።
7 ፤ የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከልም ጠብ ሆነ በዚያም ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር።
8 ፤ አብራምም ሎጥን አለው። እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ።
9 ፤ ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።
10 ፤ ሎጥም ዓይኑን አነሣ፥ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ዞዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል ነበረ።
11 ፤ ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ፤ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፤ አንዱም ከሌላው እርስ በርሳቸው ተለያዩ።
12 ፤ አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ ሎጥም በአገሩ ሜዳ ባሉት ከተሞች ተቀመጠ፥ እስከ ሰዶምም ድረስ ድንኳኑን አዘዋወረ።
13 ፤ የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ።
14 ፤ ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው። ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤
15 ፤ የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና።
16 ፤ ዘርህንም እንደ ምድር አሸዋ አደርጋለሁ፤ የምድርን አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል።
17 ፤ ተነሣ በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርስዋን ለአንተ እሰጣለሁና።
18 ፤ አብራምም ድንኳኑን ነቀለ መጥቶም በኬብሮን ባለው በመምሬ የአድባር ዛፍ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ።