ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 40

1 ፤ ከዚህ ነገር በኋላም እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ የጠጅ አሳላፊና የእንጀራ አበዛ ጌታቸውን የግብፅ ንጉሥን በደሉ።
2 ፤ ፈርዖንም በሁለቱ ሹማምቱ በጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ አበዛዎቹ አለቃ ላይ ተቆጣ፤
3 ፤ ዮሴፍ ታስሮ በነበረበትም በግዞት ስፍራ በዘበኞቹ አለቃ ቤት አስጠበቃቸው።
4 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ለዮሴፍ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ያገለግላቸው ነበር፤ በግዞት ቤትም አያሌ ቀን ተቀመጡ።
5 ፤ በግዞት ቤት የነበሩት የግብፅ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊና እንጀራ አበዛ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት እንደ ሕልሙ ትርጓሜ እየራሳቸው ሕልምን አለሙ።
6 ፤ ዮሴፍም ማልዶ ወደ እነርሱ ገባ፥ እነሆም አዝነው አያቸው።
7 ፤ በጌታው ቤት ከእርሱ ጋር በግዞት የነበሩትንም የፈርዖንን ሹማምት እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው። እናንተ ዛሬ ስለ ምን አዝናችኋል?
8 ፤ እነርሱም። ሕልምን አልመን የሚተረጕምልን አጣን አሉት። ዮሴፍም አላቸው። ሕልምን የሚተረጕም እግዚአብሔር የሰጠው አይደለምን? እስቲ ንገሩኝ።
9 ፤ የጠጅ አሳላፊዎች አለቃም ለዮሴፍ ሕልሙን እንዲህ ብሎ ነገረው። በሕልሜ የወይን ዛፍ በፊቴ ሆና አየሁ፥
10 ፤ በዛፊቱም ሦስት አረግ አለባት፤ እርስዋም ቅጠልና አበባ አወጣች፥ ዘለላም አንጠለጠለች፥ የዘለላዋም ፍሬ በሰለ፤
11 ፤ የፈርዖንም ጽዋ በእጄ ነበረ፤ ፍሬውንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ጨመቅሁት፥ ጽዋውንም ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት።
12 ፤ ዮሴፍም አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ አረግ ሦስት ቀን ነው፤
13 ፤ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ ወደ ቀደመው ሹመትህም ይመልስሃል፤ ጠጅ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ስታደርግ እንደ ነበረው እንደ ቀድሞው ሥርዓትም የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ።
14 ፤ ነገር ግን በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን አስበኝ፥ ምሕረትንም አድርግልኝ፥ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ፤
15 ፤ እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና፤ ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም።
16 ፤ የእንጀራ አበዛዎቹ አለቃም ሕልሙን በመልካም እንደ ተረጎመ ባየ ጊዜ ዮሴፍን እንዲህ አለው። እኔም ደግሞ ሕልም አይቼ ነበር፥ እነሆም ሦስት መሶብ ነጭ እንጀራ በራሴ ላይ ነበረ፤
17 ፤ በላይኛውም መሶብ ፈርዖን ከሚበላው ከጋጋሪዎች ሥራ ሁሉ ነበረበት፤ ወፎችም በራሴ ላይ ከመሶቡ ይበሉ ነበር።
18 ፤ ዮሴፍም መልሶ እንዲህ አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤
19 ፤ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ በእንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።
20 ፤ በሦስተኛውም ቀን ፈርዖን የተወለደበት ቀን ነበረ፥ ለሠራዊቱም ሁሉ ግብር አደረገ፤ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎቹን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ከፍ አደረገ።
21 ፤ የጠጅ አሳለፊዎቹንም አለቃ ወደ ስፍራው መለሰው፥ ጽዋውንም በፈርዖን እጅ ሰጠ፤
22 ፤ የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ ሰቀለው፥ ዮሴፍ እንደተረጎመላቸው።
23 ፤ የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን አላሰበውም፥ ረሳው እንጂ። a