ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 42

1 ፤ ያዕቆብም በግብፅ እህል እንዳለ ሰማ፥ ያዕቆብም ልጆቹን። ለምን እርስ በርሳችሁ ትተያያላችሁ? አላቸው።
2 ፤ እንዲህም አለ። እነሆ ስንዴ በግብፅ እንዲገኝ ሰምቼአለሁ፤ ወደዚያ ውረዱ፥ እንድንድንና እንዳንሞትም ከዚያ ሸምቱልን።
3 ፤ የዮሴፍም አሥሩ ወንድሞቹ ስንዴን ከግብፅ ይሸምቱ ዘንድ ወረዱ፤
4 ፤ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን ግን ያዕቆብ ከወንድሞቹ ጋር አልሰደደውም። ምናልባት ክፉ እንዳያገኘው ብሎአልና።
5 ፤ የእስራኤልም ልጆች ለእህል ሸመታ ከመጡቱ ጋር ገቡ፤ በከነዓን አገር ራብ ነበረና።
6 ፤ ዮሴፍም በምድር ላይ ገዥ ነበረ፥ እርሱም ለምድር ሕዝብ ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በምድር ላይ በግምባራቸው ሰገዱለት።
7 ፤ ዮሴፍም ወንድሞቹን አይቶ አወቃቸው፤ ተለወጠባቸውም፥ ክፉ ቃልንም ተናገራቸው። እናንተ ከወዴት መጣችሁ? አላቸው። እነርሱም። ከከነዓን ምድር እህል ልንሸምት የመጣን ነን አሉት።
8 ፤ ዮሴፍም ወንድሞቹን አወቃቸው፥ እነርሱ ግን አላወቁትም፤
9 ፤ ዮሴፍም ስለ እነርሱ አይቶት የነበረውን ሕልም አሰበ። እንዲህም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ፤ የምድሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል።
10 ፤ እነርሱም አሉት። ጌታችን ሆይ አይደለም፤ ባሪያዎችህ ስንዴን ሊገዙ መጥተዋል፤
11 ፤ እኛ ሁላችን የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ እኛ እውነተኞች ነን፥ ባሪያዎችህስ ሰላዩች አይደሉም።
12 ፤ እርሱም አላቸው። አይደለም፤ ነገር ግን የአገሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል።
13 ፤ እነርሱም አሉ። ባሪያዎችህ አሥራ ሁለት ወንድማማች በከነዓን ምድር የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ ታናሹም እነሆ ዛሬ ከአባታችን ጋር ነው፥ አንዱም ጠፍቶአል።
14 ፤ ዮሴፍም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ ብዬ የተናገርኋችሁ ይህ ነው፤
15 ፤ በዚህ ትፈተናላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁ ካልመጣ በቀር የፈርዖንን ሕይወት ከዚህ አትወጡም።
16 ፤ እውነትን የምትናገሩ ከሆነ ነገራችሁ ይፈተን ዘንድ ከእናንተ አንዱን ስደዱ፥ ወንድማችሁንም ይዞ ይምጣ እናንተም ታሥራችሁ ተቀመጡ፤ ይህ ካልሆነ የፈርዖንን ሕይወት ሰላዮች ናችሁ።
17 ፤ ሦስት ቀን ያህል በግዞት ቤት ጨመራቸው።
18 ፤ በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው። ትድኑ ዘንድ ይህን አድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔርን እፈራለሁና።
19 ፤ እናንተ የታመናችሁ ከሆናችሁ ከእናንተ አንዱ ወንድማችሁ በግዞታችሁ ቤት ይታሰር እናንተ ግን ሂዱ፥ እህሉንም ለቤታችሁ ራብ ውሰዱ፤
20 ፤ ታናሹንም ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ፤ ነገራችሁም የታመነ ይሆናልና አትሞቱም። እንዲህም አደረጉ።
21 ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ። በእውነት ወንድማችንን በድለናል፥ እኛን በማማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውምና፤ ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን።
22 ፤ ሮቤልም መልሶ እንዲህ አላቸው። ብላቴናውን አትበድሉ ብያችሁ አልነበረምን? እኔም አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህ እነሆ አሁን ደሙ ይፈላለገናል።
23 ፤ እነርሱም ዮሴፍ ነገራቸውን እንደሚሰማባቸው አላወቁም፥ በመካከላቸው አስተርጓሚ ነበረና።
24 ፤ ከእነርሱም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ደግሞም ወደ እነርሱ ተመልሶ ተናገራቸው፥ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ወሰዶ በፊታቸው አሰረው።
25 ፤ ዮሴፍም ዓይበታቸውን እህል ይሞሉት ዘንድ አዘዘ፤ የእየራሳቸውንም ብር በእየዓይበታቸው ይመልሱት ዘንድ ደግሞም የመንገድ ስንቅ ይሰጡአቸው ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ተደረገላቸው።
26 ፤ እነርሱም እህሉን በአህዮቻቸው ላይ ጫኑ፥ ከዚያም ተነሥተው ሄዱ።
27 ፤ ከእነርሱም አንዱ ባደሩበት ስፍራ ለአህያው ገፈራን ይሰጥ ዘንድ ዓይበቱን ሲፈታ ብሩን አየ፥ እነሆም በዓይበቱ አፍ ላይ ነበረች።
28 ፤ ለወንድሞቹም። ብሬ ተመለሰችልኝ፥ እርስዋም በዓይበቴ አፍ እነኋት አላቸው። ልባቸውም ደነገጠ፥ እየተንቀጠቀጡም እርስ በርሳቸው ተባባሉ። እግዚአብሔር ያደረገብን ይህ ምንድር ነው?
29 ፤ ወደ አባታቸውም ወደ ያዕቆብ ወደ ከነዓን ምድር መጡ፥ የደረሰባቸውንም ነገር ሁሉ እንዲህ ብለው አወሩ።
30 ፤ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው በክፉ ንግግር ተናገረን፥ የምድሪቱም ሰላዮች አስመሰለን።
31 ፤ እኛም እንዲህ አልነው። እውነተኞች ሰዎች ነን እንጂ ሰላዮች አይደለንም፤
32 ፤ እኛ የአባታችን ልጆች አሥራ ሁለት ወንድማማች ነን፤ አንዱ ጠፍቶአል፥ ታናሹም በከነዓን ምድር ዛሬ ከአባታችን ጋር አለ።
33 ፤ የአገሩም ጌታ ያ ሰው እንዲህ አለን። የታመናችሁ ሰዎች ከሆናችሁ በዚህ አውቃለሁ፤ አንደኛውን ወንድማችሁን ከእኔ ጋር ተዉት፥ ለቤታችሁም ራብ እህልን ወስዳችሁ ሂዱ፤
34 ፤ ታናሹንም ወንድማችሁን አምጡልኝ፥ እውነተኞች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁንም በዚህ አውቀዋለሁ፤ ወንድማችሁንም እሰጣችኋለሁ፥ እናንተም በምድሩ ትነግዳላችሁ።
35 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ዓይበታቸውን በፈቱ ጊዜ እነሆ ከእነርሱ እያንዳንዳቸው ብራቸውን በእየዓይበታቸው ተቋጥሮ አገኙት፤ እነርሱም አባታቸውም የብራቸውን ቍጥራት አይተው ፈሩ።
36 ፤ አባታቸው ያዕቆብም እንዲህ አላቸው። ልጅ አልባ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፥ ስምዖንም የለም፥ ብንያምንም ትወስዱብኛላችሁ፤ ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ደረሰ።
37 ፤ ሮቤልም አባቱን አለው። ወደ አንተ መልሼ ያላመጣሁት እንደ ሆነ ሁለቱን ልጆቼን ግደል፤ እርሱን በእጄ ስጠኝ፥ እኔም ወደ አንተ እመልሰዋለሁ።
38 ፤ እርሱም አለ። ልጄ ከእናንተ ጋር አይወርድም፤ ወንድሙ ሞቶ እርሱ ብቻ ቀርቶአልና፤ በምትሄዱበት መንገድ ምናልባት ክፉ ነገር ቢያገኘው ሽምግልናዬን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። a